የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ወደተሻለ ከፍታ የምንሸጋገርበት ይሁንልን::

የፋሲካ በዓል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እኛን ነፃ ያወጣበት ማስታወሻ ስለሆነ ለክርስቲያን አማኞች ትልቁ ክብረ በዓል ነው::

የፋሲካ የቃሉ ትርጉም፦ ማለፍ፣ መሻገር፣ መሸጋገር (በብሉይ ኪዳን መላእክቱ ያለፉበት በሐዲስ ኪዳን ነፃ የወጣንበት)። በአጠቃላይ ፋሲካ ማለት የነፃነት፣ የድልና ወደ አዲስ ሕይወት መሻገር በዓል ተደርጎ ይወሰዳል።

በቃሉ ትርጉም መሠረት አዳዲስ የዓመት በዓል የድግስ ወቅት ወጎችን (habits) በፋሲካና በዳግማዊ ትንሣኤ ድግስ ወቅት እንድንሞክርና እንድንተገብር እጋብዛችኃለሁ::

በፋሲካና በሌሎች አመት በዓላት ወቅት እጅግ ልቤን ከሚያሞቁት ነገራቶች ዋኖቹ ከዘመድ ወዳጅ ጋር ሰብሰብ ማለትና ኢትዮጵያውያዊ የመተሳሰብና ጨዋነት (decency) ስብዕናዎች ናቸው::

እባካችሁ አትኮንኑኝና ትናንት በዋሺግተን ዲሲ አካባቢ በሠፈሬ ካለና ከምወደው መሸታ ቤት ሳለሁ Bob ከተሰኘ ፈረንጅ ጋር ተዋዉቀን ስናወጋ ኢትዮጵያውያዊ መሆኔን ሲያውቅ የተዋወቃቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ጨዋ መሆናችንን አረጋገጠልኝ:: ጎረቤቱ ኢትዮጵያዊ ለአሁኑ ፋሲካ ቤቱ እንደጋበዘው በደስታና በሞቅታ አበሰረልኝ:: ሙገሳውን በሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ስም እንደምርቃት አሜን ብዬ ተቅብዬ ይህችን መልዕክት አዘጋጅቼ ላካፍላችሁ ወሰንኩ::

ይህንን ፋሲካ ስናከብርና ሰብሰብ ስንል ሁለት የቤት ሥራ ልስጠን ወስኛለሁ:: (1ኛ) ለፋሲካና ለዳግማዊ ትንሣኤ ለድግስ ስንሰባሰብ ራሳችንን ከመውቀስ ተቆጥበን ዓለም በሚያውቅልን ጨዋነት (culture of decency) ራሳችንን በፈገግታ እናንቆለፖጵስ 😂 (2ኛ) 99% የፋሲካን ድግስ የደገሱ ሴቶቻችን ስለሆኑ ያ ሁላ ምግብ ከስማይ እንደመና የወረደ ሳይሆን በሴቶቻችን ድካምና እንቅልፍ ማጣት የተዘጋጀ መሆኑ ታውቆ (ሀ) ምግቡን በጸሎት ስንባርክ ፈጣሪንም የደከሙትን ሴቶችም በስም ጠርተን እናመስግን :: እንመርቅ:: (ለ) የድግስ ምግብ ስንበላ ከሌላ ወሬ ተቆጥበን ምግቡን በያይነቱ እየጠቃቀስን እናድንቅ:: ይሐ ለጤናችም ጥሩ ነው:: (ሐ) ከድግሱ በኃላ ወንዶቹ ሽሚዛችንን ሰብስበን በትብብርና በደስታ በሳህን አጠባና ቤት ጽዳት እንረባረብ:: ሴቶቹ ዘና እንዲሉ ፋታ እንስጣቸው::

ግብዝ (hypocrite) እንዳትሉኝ:: ዛሬ እኔና ቤተሰቤ ከምንውዳቸው ከጎረቤቶቻችን ከሰለሞንና ሃይማኖት ቤት ለፋሲካ ግብዣ ከቀሩት ከምንውዳቸው ጎረቤቶቻችን ጋር በምንታደምበት ወቅት እነዚህን የፈጠርኳቸውን ትዕዛዛት ለመተግበር ተዘግጅቻለሁ:

የጠቀስኳቸውን የዓመት በዓል ድግስ ወጎች (habits) የሙከራ ልምዳችሁን እንድታካፍሉን እጋብዛለህ::

የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ወደተሻለ ከፍታ የምንሸጋገርበት ይሁንልን:: አሜን::

ከጠለቀ ፍቅር ጋር::
❤️ ❤️❤️
ከጌብ ሐምዳና ቤተሰቡ